የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ የሰላም ጉባዔ ተሳታፊ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ጎበኙ

By ዮሐንስ ደርበው

November 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አኅጉር አቀፍ የአፍሪካ የሰላም ጉባዔ ተሳታፊ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎችን ጎበኙ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ለጎብኚዎቹ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት÷ ተቋሙ በ2022 በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት አንዱ ለመሆን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ፤ አካታች እና በሕዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት ተፈጥሮ ማየት የሚለውን ራዕይ ሰንቆ በቁርጠኝነት ተቋማዊ ሪፎርም እየተገበረ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ ሪፎርሙን ለመተግበር በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እየተመራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ መረጃ መር እና ማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል መርኅን የሪፎርሙ አካል አድርጎ ውጤታማ የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ ሥራዎችን እያከናወ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ጎብኚዎቹ በቅርቡ የተመረቀውን የፎሬንሲክ ሳይንስ ኢንስቲትዩት የምርምር ልኅቀት ማዕከልን መመልከታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በግንባታ ላይ የሚገኘውን የኢንተርናሽናል ፖሊስ ሊደርሽፕ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች የሪፎርም ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡