አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለቀጣይ አራት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የሚወዳደሩ አምስት የመጨረሻ ዕጩዎች ይፋ ሆነዋል።
በዚሁ መሠረት ከትግራይ ክልል አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም፣ ከአማራ ክልል አቶ ያየህ አዲስ፣ ከኦሮሚያ ክልል አትሌት ስለሺ ስኅን፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮ/ር ግርማ ዳባ፣ ከድሬዳዋ አሥተዳደር አቶ ጌቱ ገረመው እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አቶ ዱቤ ጅሎ ፌደሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት በዕጩነት ቀርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ለሥራ አስፈፃሚ አባልነት ዕጩዎች ይፋ የተደረጉ ሲሆን÷ ሶማሌ ክልል ምንም ዓይነት ዕጩ እንዲሁም ድሬዳዋ አሥተዳደር ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዕጩ ሳያቀርቡ ቀርተዋል፡፡
እንዲሁም ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ እና ሐረሪ ክልሎች ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሁለት ሁለት ዕጩ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ማቅረብ የቻሉት አንድ አንድ ብቻ ነው፡፡
በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርን ጨምሮ ከላይ ከተገለጹት ውጭ ያሉት ክልሎች ሁለት ሁለት ዕጩዎችን አቅርበዋል።
የፕሬዚዳንት እና የሥራ አስፈፃሚ ምርጫው በመጪው ታኅሣስ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው የፌዴሬሽኑ 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡