አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተዛባ መረጃ ስደተኞችን ከመነሻው ጀምሮ መደበኛ ያልሆኑ መንገዶችን እንዲከተሉ እንደሚያደርግ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ፡፡
በጄኔቫ በተካሄደው የ2024 ዓለም አቀፍ ፍልሰት ላይ ትኩረቱን ባደረገ ውይይት የሀሰተኛ መረጃን በመዋጋት ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መደበኛ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እውን ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች የሀሰተኛ መረጃ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ዘርዝረዋል።
በትውልድ ሀገራት ያለው የሀሰት መረጃ ባህሪም በዋናነት በመዳረሻ ሀገራት ያሉትን እድሎች አጋንኖ በመግለጥና ስደተኞች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በማቅለል የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመዳረሻ ሀገራት ያለው የተዛባ መረጃም የስደተኞች ስጋት፣ የፖለቲካ ጽንፈኝነትና ጥላቻን የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የሀሰት መረጃን ለመዋጋት የሚዲያ ሚና እና አስተማማኝ መረጃ የመንግስት ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ረገድ ስላላቸው የጎላ ሚናም አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሥራና ክኅሎት ሚኒስቴርን በማቋቋም ፍላጎትና አቅርቦትን የሚያስተሳስር የሠራተኛ መረጃ ሥርዓት በመዘርጋት የወሰደችው ጠቃሚ ርምጃ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሕጋዊ መንገዶችን እንዲመርጡ ማስቻሉን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች እንደምትገኝም አስታውቀዋል፡፡