Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አየር ኃይሉ በበርካታ ጀግኖች መስዋዕትነት የፀና ታላቅ ተቋም ነው -ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ አየር ኃይል በበርካታ ጀግኖች መስዋዕትነት የፀና ታላቅ ተቋም ነው ሲሉ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

“የተከበረች ሀገር የማይደፈር አየር ኃይል” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን 89ኛው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ቀንን አስመልክቶ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ አየር ኃይል ተመስርቶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በርካታ ጀግኖች ላባቸውን እና ደማቸውን ከማፍሰስም በላይ ውድ ህይወታቸውን ሰውተው ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር ማድረግ ችለዋል ብለዋል፡፡

በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰውን አየር ኃይል ይበልጥ በማዘመንና ለታላቅ ሀገር የሚመጥን አየር ኃይል ገንብተን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማሸጋገር በሁሉም ዘርፉ እየሰራን እንገኛለንም ነው ያሉት።

ተቋሙ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከመፍጠር ጀምሮ የአባላቱን አቅም በስልጠና ለማዳበር ብሎም በራስ አቅም ታላላቅ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም መግለፃቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለይም ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠርና በሁሉም መስክ ዝግጁ እና ቀልጣፋ የሆነ ሠራዊት በመገንባት ለታላቅ ሀገር የሚመጥን ታላቅ አየር ኃይል እየተገነባ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

አየር ኃይሉ ወቅቱ የሚጠይቀውን የውጊያ መሠረተ ልማት በማሟላት እና የትጥቆችን አቅም በማዘመን የኢትዮጵያን የአየር ክልል ከየትኛውም ጥቃት በንቃት እየጠበቀ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

 

 

Exit mobile version