የሀገር ውስጥ ዜና

እንደሀገር በመሠረተ-ልማት ዘርፍ ጉልህ እድገት ተመዝግቧል- ፕሬዚዳንት ታዬ

By ዮሐንስ ደርበው

November 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ መሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ማዕቀፍ ኢትዮጵያ በዘርፉ ጉልህ እድገት ማስመዝገቧን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡

“ለአፍሪካ ዘላቂ እድገት የሚሆን ጠንካራና ሁሉን አሳታፊ የሆነ መሠረተ-ልማት መገንባት” በሚል መሪ ሐሳብ የአፍሪካ መሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የውይይት መድረክ ፕሬዚዳንቱ በተገኙበት ዛሬም ቀጥሏል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ያጋሩት ፕሬዚዳንት ታዬ÷ በመንገድ አውታሮች፣ በባቡር ሀዲዶች እና በታዳሽ ኃይል ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶች የሀገራችንን የመሠረተ-ልማት ሥርዓት ቀይሮታል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ-ጅቡቲ ባቡር ሀዲድ የአካባቢውን ግንኙነት በማጠናከር የትራንስፖርት ወጪን በመቀነስና ንግድን በማበረታታት ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አንስተዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለዘላቂ ኃይል ለመጠቀም ያለንን ቁርጠኝነት ያሳየንበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ንጹህ ኃይል በማቅረብ የሚረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ መሠረተ-ልማት ማስፋፊያ የአጀንዳ 2063 ዐበይት ግቦችን ለማሳካት እያከናወንን ባለው ሥራ ዋና ዓምድ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ይህ ፕሮግራም በድንበር ተሻጋሪ የመሠረተ-ልማት ላይ ያተኮረ፣ ለቀጣናዊ ውኅደት፣ ለኢኮኖሚያዊ እድገት እና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ አማካኝነትም በአፍሪካ ሀገራት መካከል ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር፣ የአፍሪካ እርስ በርስ ንግድን ለማሳደግ እና ዘላቂ ብልፅግናን ለመደገፍ የሚያስችል መሠረተ-ልማት ለመፍጠር እንጥራለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

በፍሬሕዎት ሰፊው