ስፓርት

ዛምቢያዊቷ ባርብራ ባንዳ የዓመቱ ምርጥ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋች ተሸላሚ ሆነች

By ዮሐንስ ደርበው

November 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዛምቢያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና ኦርላንዶ ፕራይድ እግር ኳስ ክለብ የፊት መስመር ተጫዋች ባርብራ ባንዳ የ2024 የቢቢሲ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማትን አሸነፈች፡፡

የስፔን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና የባርሴሎና አጥቂ አይታና ቦንማቲ እንዲሁም ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና ሳን ዲያጎ ተከላካይ ናኦሚ ግርማ ባለፈው ወር ይፋ በተደረገው የመጨረሻዎቹ አምስት ዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ይታወሳል፡፡

በዚህ ምርጫ ተሳታፊ የነበሩት የእግር ኳስ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ የእግር ኳስ አመራሮች እና ጋዜጠኞች የ2023/24 የውድድር ዘመን ስኬትን ከግምት አስገብተዋል ተብሏል፡፡

በፓሪሱ ኦሊምፒክ ባርብራ ባንዳ ለሀገሯ አራት ግቦችን ያስቆጠረች ሲሆን÷ በአፍሪካ አኅጉር በኦሊምፒክ መድረክ 10 ግቦችን በማስቆጠርም ቀዳሚ ነች፡፡

ለኦርላንዶ ፕራይድ ባለፈው ዓመት ፊርማዋን ካኖረች ወዲህም 13 ግቦችን ማስቆጠር ችላለች፡፡

ተጫዋቿ ለመራጮቿ ብሎም ለቤተሰቧ እና ለክለብ አጋሮቿ ምስጋና በማቅርብ በዛምቢያ ተወልዶ በሴቶች እግር ኳስ ለዚህ ስኬት መብቃት ከባድ ነው ሆኖም ግን አድሬጌዋለው ብላለች፡፡

በቀጣይ ጠንክራ በመሥራት የላቁ ስኬቶች እንደምተስመዘግብ እምነቷን ገልጻለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡