Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በዓለም መድረክ የአፍሪካን ድምጽ ለማሰማት ቀጣይነት ያለው ጥረት እንዲደረግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ መድረኮች የአፍሪካን ድምጽ ለማሰማት ቀጣይነት ያለው ጥረት እንዲደረግ  የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ጠይቋል፡፡

በ23ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ተሳትፏል።

ስብሰባው በዚህ ዓመተ በጋና አክራ የተካሄደው 45ኛው መደበኛ ጉባኤ ባወጣው መመሪያ መሰረት የአፍሪካ ህብረት የክህሎት ምዘና እና የብቃት ኦዲት አፈፃፀም(ሳካ) ሂደት ከኦዲት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መፍታትና የአፍሪካ ህብረት በቡድን-20 ቋሚ አባልነቱ የአፍሪካን ስትራቴጂካዊ ቀዳሚ ጉዳዮች አስመልክቶ ግምገማ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በስብሰባው የአፍሪካ ህብረት የክህሎት ምዘና እና የብቃት ኦዲት አፈፃፀም ሂደት ላይ ሰፊ ውይይቶች ተካሂዷል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በጉዳዩ ላይ ከዚህ ቀደም የተላለፉ የፖሊሲ ውሳኔዎችን መከተል አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የክህሎት ምዘና እና የብቃት ኦዲት አፈፃፀም በክህሎት እና በብቃት ላይ የተመሰረተ የውስጥ ሰራተኞችን ወደ ስራ ለማሰማራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተነደፈ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኮሚሽኑን የአሰራር ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ለማሳደግ አፈፃፀሙን ማፋጠን እንደሚያስፈልግም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ጉባኤው በፈረንጆቹ በዚህ ዓመት በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው የቡድን-20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ የህብረቱን ተሳትፎ አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርት ገምግሟል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ መድረኮች የአፍሪካን ድምጽ ለማሰማት ቀጣይነት ያለው ጥረት እንዲደረግ ልዑካኑ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ጉባኤው የተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት ውስጣዊ ሂደቶቹን ለማጠናከር እና ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ የተለያዩ ቁልፍ ውሳኔዎችን በማሳለፍ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

 

Exit mobile version