የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ ለምን አስፈለገ?

By ዮሐንስ ደርበው

November 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄድ ሁለት መነሻ ምክንያቶች መኖራቸው ይነገራል፡፡

እነዚህ መነሻ ምክንያቶችም ቀጥለው የተገለጹት መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

  1. በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነት እና አለመግባባት መኖሩ ነው።
  1. ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

በአጠቃላይ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመነሳትና የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በማጥናት በኢትዮጵያ የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያበረታታል ብሏል ኮሚሽኑ።

ስለሆነም የሚስተዋሉትን ሰፍፊና ዘርፈ-ብዙ ልዩነቶች ለመፍታት አካታች የሆኑ የህዝብ ምክክሮችን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ በሀገራችንም ውስጥ ይህንን ለማስጀመር ወደ ሥራ ተገብቷል ብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር ምክክሩ የሀገራችንን ጥቅም ማስቀደምን እና ሀገር በቀል እውቀቶችን መጠቀምን እንደ መሠረታዊ መርሆቹ አድርጎ ስለሚወስድ ሂደቱን ከውጭ ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያለው፡፡

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!