አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ከአኅጉር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ጎን ለጎን በደቡብ ሱዳን የሰላም ግንባታ ሚኒስትር እስቴፈን ፖን ኮል ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት የድንበር አካባቢ ሰላም፣ ልማት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በስፋት ወሰን የሚጋሩ ሀገራት እንደመሆናቸው የሀገራቱ ሕዝቦች ግንኙነትን ማጠናከርን ጨምሮ የልማት፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ የጋራ ተጠቃሚነት በውይይቱ መነሳቱን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በወሰን አካባቢ የሚኖሩ የሀገራቱን ዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሠነድ በማዘጋጀት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡