Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ እና ሕንድን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ሕንድን በርካታ ዘመናት ያስቆጠረ ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት በይበልጥ በተለያዩ ዘርፎች ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተደረገ፡፡

በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻወል የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሕንድ ፕሬዚዳንት ዶውፓዲ ሙርሙ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት አምባሳደሩ ከፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕንድ ፕሬዚዳንት የተላከውን መልዕክት አድርሰዋል፡፡

አምባሳደሩ ከፕሬዚዳንቷ ጋር ባደረጉት ውይይትም በኢትዮጵያና ሕንድ መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና በሰው ሃብት ልማት ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት መኖሩ ተነስቷል፡፡

በቀጣይም የጋራ ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን÷ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፎች ላይ በይበልጥ ትብብሮችን ማሳደግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

Exit mobile version