Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የልማት አጋሮች በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል – አፈ ጉባዔ ታገሰ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አህጉራዊና ዓለም አቀፍ አጋሮች በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማጎልበት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ጠየቁ።

“የበለጸገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የተካሄደው የመጀመሪያ ቀን የውይይት መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የተገኙት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ÷ ሰላም ከፍ ያለ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰባችን እድገት፣ ብልጽግና እና ደህንነት መሰረታዊ ፍላጎት ነው ብለዋል።

በዚህም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ አጋሮች በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማጎልበት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

የአፍሪካን ችግሮች በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለመፍታት የጋራ ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ጉባዔ ማጠቃለያ ሳይሆን አዲስ ጅምር ነው ያሉት አፈ ጉባዔው÷ እጅ ለእጅ ተያይዘን የበለጸገች እና ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን በጋራ ለመገንባት የገባነውን የጋራ ቃል ኪዳን የምናድስበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬ የምናደርጋቸው የጋራ ተግባራት የመጪውን ትውልድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርጹ መሆኑን አውቀን ውይይትን፣ እርቅን እና ትብብርን ለማጎልበት በምናደርገው ጥረት በአንድነት መቆም አለብን ማለታቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአህጉሪቱ ዘላቂ ሠላም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

Exit mobile version