አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት 5 ዓመታት መሠረታዊ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል መጠነ ሰፊ ስራዎችን ሰርቷል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡
በክልል ደረጃ የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና “! በሚል መሪ ሃሳብ በቦንጋ ከተማ የማጠቃለያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ÷ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ በጀመረችው የለውጥ ጉዞ ውስጥ መሠረታዊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል መጠነ ሰፊ ስራዎች ሰርቷል ብለዋል።
ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ ህብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ገዢ ብሔራዊ ትርክት ለመገንባት ፈር ቀዳጅና ሀገር በቀል አስተሳሰብ የሆነውን የመደመር ዕሳቤ ዕዉን በማድረግ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የብዝሃ ክፍለ ኢኮኖሚ ልማት ፈለግ በመከተል በግብርና ኢንዱስትሪ ፣በማዕድን፣ በቱሪዝም፣በቴክኖሎጂ እና በሌሎችም ዘርፎች አበረታች ተግባራት መከናወናቸውንም መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የጸጥታ ስራዎችን በዘላቂነት ማስቀጠል፣የዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ፣የትምህርት ጥራት ማስጠበቅና በሽታን መከላከል መሠረት ያደረጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡