Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ተመድ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ሰላም የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ የተመድ ረዳት ዋና ጸሀፊ እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ ዶ/ር ገለጹ።

የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፈረንስ “የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት ራሚዝ አላክባሮቭ ዶ/ር፤ ኮንፈረንሱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራትና ለአህጉሪቱ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው ድርጅታቸው የኢትዮጵያን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የዓለምን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የአፍሪካን ሰላም መጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ በጋራ ተባብሮ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቷን ሰላም ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካሳየው ቁርጠኝነት ባሻገር በሽግግር ፍትህ አማካኝነት ዘላቂ ፍትህና ሰላምን ለማረጋገጥ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ከፍተኛ በጀት መድቦ ወደ ተግባር መግባቱንም አድንቀዋል፡፡

Exit mobile version