ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሂዝቦላህ በሚሳኤሎችና ድሮኖች በመታገዝ እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጸመ

By Melaku Gedif

November 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሂዝቦላህ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሚሳኤሎችና ድሮኖች በመታገዝ እስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በእስራኤል እና በሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦህ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ ተመላክቷል፡፡

ከሰሞኑ እስራኤል በሊባኖስ መዲና ቤሩት የተለያዩ አቅጣጫዎች በተመረጡ የሂዝቦላህ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በጥቃቱ እየደረሰ ያለውን ውድመት ተከትሎም በቤሩት እስከ ቀጣዩ ጥር ወር ድረስ ት/ቤት መዘጋቱን የሊባኖስ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ለጥቃቱ አጸፋም ሂዝቦላህ 340 በሚሆኑ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙ ነው የተገለጸው፡፡

በጥቃቱም በሰሜንና ማዕከላዊ እስራኤል በርካታ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን÷ ህንጻዎችና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውም ተጠቁሟል፡፡

እስካሁን ድረስ በ11 ሰዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት መድረሱን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡

በጥቃቱ ከደረሰው ውድመት ባሻገር በሚሊየን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ከጥቃቱ ሽሽት ወደ ምሽግ መግባታቸው ተጠቁሟል፡፡