Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በየዕለቱ ከ800 የሚልቁ ተማሪዎችን የሚመግቡት መምህርት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መምህርት ቢርቂሳ ጀማል ላለፉት አራት ዓመታት ያለማቋረጥ ከ800 በላይ ተማሪዎችን በግላቸው በቀን አንድ ጊዜ እየመገቡ ይገኛሉ፡፡

መምህርቷ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ በሚገኘው ጅሬን ቁጥር ሁለት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ሙያ በማገልገል ላይ ሲሆኑ÷ ትውልድን በዕውቀት እና ሥነ-ምግባር ማነጽ የሠርክ ሥራቸው ነው፡፡

መደበኛ ሥራቸው ከሆነው ማስተማር ጎን ለጎንም ፈታኙን የኑሮ ውድነት ተቋቁመው ላለፉት አራት ዓመታት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖች ልጆች የሆኑ ተማሪዎችን በመመገብ ሰብዓዊ ተግባር ይከውናሉ፡፡

ይህን በጎ ተግባር ለመጀመር ምን እንዳነሳሳቸው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለቀረበላቸው ጥያቄ÷ “አንድ ተማሪ ራሱን ስቶ ወደቀ፤  ከነቃ በኋላ ሲጠየቅ እራትም ሆነ ምሳ አለመብላቱን ሰዎች ነገሩኝ፤ ከልቤ አዘንኩ፤ ይህ ታሪክ የበርካቶች ሊሆን ስለሚችል ከቤተሰቦቼ ጋር በመወያየት ለተማሪዎች ምግብ ማቅረብ እንዳለብን ወሰንን” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ባሕር ማዶ የምትኖረው የአብራካቸው ክፋይም ይህን በጎ ተግባር በመደገፍ በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግላቸው ይናገራሉ፡፡

ምገባው የተማሪዎችን ከትምርህት መቅረት ማስቀረቱን፣ በትምህርታቸው ላይም አበረታች ውጤት ማምጣቱን እና የተወሰነ የቤተሰብ ጫና መቀነሱን መምህርት ቢርቂሳ እና የተማሪዎቹ ወላጆች ይናገራሉ፡፡

መምህርቷ ካለብኝ የኢኮኖሚ አቅም አኳያ እንጅ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ የማቀርበው የሚደግፈኝ አካል ባገኝ ተማሪዎቹን በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ እፈልጋለሁ ይላሉ፡፡

የአካባቢው አሥተዳደር እና ሌሎች ግብረ-ሠናይ ድርጅቶችም የመምህርት ቢርቂሳን በጎ ተግባር በመደገፍ ቢተባበሩ “50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለ50 ሰው ጌጥ ነውና” ችግሮችን ማቅለል ይቻላል፡፡

መምህርቷ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ያደረጉትን ቆይታ በዚህ ማስፈንጠሪያ መመልከት ይችላሉ፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=igrak-MMX50

በወርቃፈራሁ ያለው

Exit mobile version