አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር ለመስራት መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ካደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ኦርዲን በድሪ በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ከተመራው የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በጽ/ቤታቸው ባደረጉት ውይይት÷ የቱሪዝም ልማት ክፍተቶችን መሙላት፣የመዳረሻ ልማት ስራዎችን ማስተዋወቅና መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
አምባሳደሮቹ በውይይቱ÷ ሀገራቱ ከክልሉ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር በቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ ተቀራርበው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
በተለይ በክልሉ ያለውን ዕምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት በመደገፍ እና በማስተዋወቅ ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን ጥቅም ማስገኘት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልፀዋል።
በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማቶች እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችሉ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
አምባሳደሮቹ በቀጣይ በሀገራቸው የሚገኙ ባለሀብቶች በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
ክልሉ የቱሪዝም መዳረሻ እንደመሆኑ በክልሉ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባት ቢቻል የቱሪስቶች ጊዜን በመቆጠብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው የከተማዋን ዕድሜ የሚመጥን ዕድገት እዉን ለማድረግ የኮሪደርና መልሶ ማልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀው ይህም የጀጎል ቅርስን መልሶ በማልማት ለቱሪስቶች ምቹ በማድረግ ህልውናውን ማስጠበቅ መቻሉን ጠቁመዋል።
በቱሪዝም፣ በሆቴል እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መንግስት አስፈላጊውን ማበረታቻ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ ማረጋገጣቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።