የሀገር ውስጥ ዜና

በመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ያለው ስራ ትልቅ እመርታ ነው – አቶ ጌታቸው ረዳ

By Mikias Ayele

November 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ያለው ስራ ትልቅ እመርታ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

በክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የቦርድ ሰብሳቢ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ እና የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንዲሁም ሌሎች የፌደራልና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ አቶ ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት፥ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽንና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እየሰሩት የሚገኘው የመልሶ ማቋቋም ስራ ከጦር መሳሪያ ማስፈታት ባለፈ የትግራይ ክልልን ሰላምና ደኅንነት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ የሚከናወን ነው።

የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ የሚገኘው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅንጅት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አዎንታዊ ውጤቶች እያመጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ጉዳይ ቀሪ ስራ እንደሚጠይቅ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችም ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ የሚገኘው ጥረት ትልቅ እመርታዊ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የተሀድሶ ስልጠና እና መልሶ ማቋቋም ተግባሩም በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ የሚያጋጥሙ የሀብት ውስንነቶችን ታሳቢ በማድረግ በኃላፊነት ስሜት መምራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም የሁሉም አይነት የልማትና የሰላም አማራጭ አቅም ተደርጎ የሚሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽንም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት አጋሮችና ተባባሪ አካላት ጋር በመተባበር ሂደቱን በውጤት ለመምራት የሄደበት ርቀት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።