የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል 17 ሺህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባቸው ተገለጸ

By Meseret Awoke

November 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አምስት ዓመታት 17 ሺህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ ከለውጡ ወዲህ በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የቢሮው ኃላፊ አህመድ ኢድሪስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ 1 ትሪሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 27 ሺህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በክልሉ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶችም ለ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ተኪ ምርቶችን በስፋት ማምረትና የኤክስፖርት መጠንን ማሳደግ ችለዋል ነው ያሉት፡፡

በኢኮኖሚ፣ ግብርና እና ፖለቲካ መስኮች የተመዘገቡ ድሎችን ጨምሮ በማህበራዊ መስኮች የክልሉን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል በተሠሩ ሥራዎች የተገኙ ስኬቶችን አብራርተዋል፡፡

እነዚህና ሌሎችም ሐሳብን በተጨባጭ ወደ ተግባር በመቀየር የተገኙ ስኬቶች ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት ዕውን ያደረጋቸው ናቸው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በሚያደርገው ከፍተኛ ድጋፍ ኢንዱስትሪዎቹ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውንም አንስተዋል፡፡

ፓርቲው እነዚህን ስኬቶችን ለማስቀጠልና ብልፅግናን እውን ለማድረግ አበክሮ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

በመራኦል ከድር