በኦሮሚያ ክልል 337 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው የመኸር ወቅት 337 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ሲል የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ በመኸር እርሻ ልማት ሥራ 11 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር መሬት በ68 የሰብል ዓይነቶች መሸፈኑን በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር ሙስጠፋ ሁሴን ተናግረዋል፡፡
በሰብል ከተሸፈነው ውስጥ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታሩ የስንዴ ልማት መሆኑን ገልጸው÷ ከዚህም 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የምርት ብክነት እዳይኖርና ምርታማነት እዲረጋገጥ እየተሠራ ባለው ሥራ በክልሉ ያሉ 600 ኮምባይነሮች እና 5 ሺህ 900 የመሬት ማለስለሻ ትራክተሮች እገዛ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የምርጥ ዘር እጥረትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አንስተው÷ ለአብነትም የስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ባቄላ ምርጥ ዘር በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እየለማ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው÷ ከእራስ ፍላጎት አልፎ ስንዴን ወደ ውጭ በመላክ የተገኘውን ስኬት በሰብሎች ላይም መድገም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በቅንጅት ለአንድ ሀገር በትጋት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በፈቲያ አብደላ