Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በመቐለ ከተማ ተካሄደ፡፡

በመርሐ-ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ተሀድሶ የቦርድ ሰብሳቢ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄነራል ፃድቃን ገብረ-ትንሳኤ እና የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የዲሞብላይዜሽን ማዕከል ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋይ ሊላይ፣ የአፍሪካ ሕብረት ተወካይ ሜጀር ጄኔራል ራዲና ስቴፈን፣ የአውሮፓ ሕብረት የለጋሽ ሀገራት አምባሳደሮች ተወካይ ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር፣ በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት ተወካይ ሳሙኤል ገባይዴ ዶ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመርሐ-ግብሩ ተጠቃሚ የቀድሞ ታጣቂዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በዝግጅቱ የታደሙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአሕጉራዊና ዓለም አቀፍ ተወካዮች የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ለመስጠት የተደረጉ የዝግጅት ሂደቶችን በመቐለ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና እና የመልሶ ማቋቋም (ዲሞብላይዜሽን) ሂደትም በመጀመሪያው ቀን ቅደመ-መረጃ (ኦረንቴሽን)፣ ምዝገባ የማካሄድና የማረጋገጥ፣ የጤና ምርመራ የማካሄድና ግብዓት የማቅረብ ስራ የሚሰራ ሲሆን ፥ በ2ኛና 3ኛው የስልጠና ቀናትም የማኅበራዊና የሥነ-ልቦና ግንባታ ትምህርት ይሰጣቸዋል።

በ4ኛው ቀን መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርትና ስልጠና፥ በ5ኛው ልዩ መታወቂያ ካርድ የመስጠት፣ የዘላቂ መቋቋሚያ ገንዘብ ክፍያ በመስጠት ስለቀጣይ ህይወት መረጃ (ኦረንቴሽን) የሚሰጣቸው ይሆናል።

በ6ኛው የተሀድሶ ስልጠና እና የመልሶ ማቋቋም (ዲሞብላይዜሽን) ቀንም ስልጠና ሲሰጥበት የቆየውን ማዕከል በማጽዳት ሰልጣኞች ወደየአካባቢያቸው ሔደው ማኅበረሰቡን በመቀላቀል መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ የሚደረግበት ዝግጅት በመርሐ-ግብሩ መቀመጡን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

ባሳለፍነው ሐሙስ ሕዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያስረከቡ 320 የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ መቐለ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከል የማስገባት ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች በመቐለ፣ እዳጋሀሙስና ዓድዋ ማዕከላት የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና የሚወስዱ ሲሆን ፥ በሚቀጥሉት አራት ወራትም በሶስቱ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከላት 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ በዘላቂነት በማቋቋም ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ የማድረግ ስራ የሚቀጥል ይሆናል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.