የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት አርሶ አደሩን በይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተመላከተ

By Meseret Awoke

November 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገበያ ሰንሰለቱን በማሻሻል አርሶ አደሩን በይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በባሌ ዞን አገርፋ ወረዳ የሌማት ትሩፋት እና የመኸር ወቅት የግብርና ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በዞኑ 578 ሺህ ሄክታር በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን እና ከዚህ ውስጥ 343 ሺህ ሄክታሩ የስንዴ ሰብል መሆኑን የገለጹት የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አሊይ መሀመድ ÷ 14 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

የምርት ብክነት እንዳይኖርም በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው÷ የአርሶ አደሩ ግንዛቤም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የመንግሥት አቅጣጫ መሆኑን አስገንዝበው ÷ የገበያ ሰንሰለቱን በማሻሻል አርሶ አደሩን በይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

እንዲሁም አርሶ አደሩ በሀገር ደረጃ በክላስተር በማረስ ምርታማነትን በይበልጥ እንዲያረጋግጥ ይሠራል ብለዋል፡፡

ዛሬ ጉብኝት በተደረገበት ወረዳም የእንስሳት ሕክምናና ማዳቀልን ጨምሮ በእንስሳት ልማት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ምልከታ ተደርጓል፡፡

በፈቲያ አብዳለ