አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ዓለም ላይ ላሉ የፖሊስ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም የማጠቃለያ፣ የዕውቅና እና የምስጋና መርሐ-ግብር አካሂዷል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በዚሁ ወቅት ÷ ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የፖሊስ ተቋማት ደረጃን ያሟላ እና የጥናትና የምርመር አቅሙን በማሳደግ ዘመኑን የሚመጥን የምርመራ አቅም የሚያጎለብት የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ገንብቶ ሥራ ማስጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት በሰጠው ትኩረት ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካ ሀገራት የስልጠና እና የምርምር ማዕከል የሚሆን አቅም የፈጠረ ተቋም ሆኗል ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ዘመኑን የሚመጥን የፖሊስ የስልጠና ተቋም እንዲሆን እየተሠራ ያለው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ሊደርሺፕ ኢንስቲቲዩት ግንባታ ሲጠናቀቅም ÷ ዓለም ላይ ላሉ የፖሊስ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቁመዋል፡፡