አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያ ይፋ ተደርጓል።
የኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን አካል የሆነው ሲምፖዚዬም እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩትና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያ (ማኑዋል) ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያው የከተሞቹን የኮሪደር ልማቶችን እንዲሁም የሳይክልና የእግረኛ መንገዶችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
መመሪያው የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሳይክልና የእግረኛ መንገድ በማስፋት የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ ዴንጌ ቦሩ በዚሁ ወቅት ÷ኢትዮጵያ ዘላቂ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮት የሆነውን የአየር ብክለትን ለመከላከል በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ የትራንስፖርት አማራጮችን መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል በመጠቀም የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የአረንጓዴ ስትራቴጂ ነድፋ በትኩረት እየሰራች እንደሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።