Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ480 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የእምነበረድ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓድዋ ከተማ በ480 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የእምነበረድ ፋብሪካ በታሕሳስ ወር የሙከራ ምርት እንደሚጀምር ተገልጿል።

በዓድዋ ኢንዱስትሪ ዞን ስር የሚገኘው ፋብሪካው በ2 ሺህ 421 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መሆኑ ነው የተመላከተው፡፡

የእምነበረድ ፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋይ ገብረ ህይወት፥ የፋብሪካው ግንባታ ሒደት 75 በመቶ መድረሱንና በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ላይ የሙከራ ምርት ማምረት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ግንባታው በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተከናወነ ሲሆን÷ለ120 ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው በክልሉ ጭላ ወረዳ ለምርት ግብዓት የሚያውለውን ጥሬ ዕቃ እንደሚያገኝ ገልጸው፥ በቅርብ ቀን የግራናይት እምነበረድ ማምረት ይጀምራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በየቀኑ በአንድ ፈረቃ 1 ሺህ 200 ሜትር ኩብ እምነበረድ ያመርታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡

Exit mobile version