Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መልስ ዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መልስ በዛሬው ዕለት በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በዚህም መሠረት ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኤቲሃድ የሰሜን ለንደኑን ቶተንም ሆትስፐርስ ከምሽቱ 2:30 ጀምሮ የሚያስተናግድበት ግጥሚያ በጉጉት ይጠበቃል።

የዛሬው ጨዋታ ለፔፕ ጓርዲዮላው ማንቼስተር ሲቲ በሁሉም የውድድር ዓይነቶች ከአራት ተከታታይ ሽንፈት መልስ የሚደረግ ሲሆን÷ ከመሪው ሊቨርፑል ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ ወደሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።

በሌላ መርሐ-ግብር የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ዘንድሮ በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኘውን ኖቲንግሃም ፎረስት አመሻሽ 12 ሰዓት ጀምሮ በሜዳው ኤሚሬትስ ያስተናግዳል።

ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ነጥቦችን የጣሉት መድፈኞቹ ወደአሸናፊነት ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት ዘንድሮ ሳይጠበቅ በጥሩ አቋም ላይ ከሚገኘው ኖቲንግሃም ፎረስት ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ይገመታል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በ11 ጨዋታዎች እኩል 19 ነጥቦችን ሲሰበስቡ÷ መድፈኞቹ ደግሞ የተሻለ የግብ ልዩነት በመያዝ በ4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ኖቲንግሃም ፎረስት በአንፃሩ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሌላ ጨዋታ 19 ነጥብ እና በ8 የግብ ልዩነት በደረጃ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ላይ የሚገኘው የምዕራብ ለንደኑ ቸልሲ ወደሌስተር ተጉዞ ከቀኑ 9:30 ጀምሮ ሌስተር ሲቲን ይገጥማል።

በሌሎች የዛሬ ግጥሚያዎች አስቶንቪላ ከክሪስታል ፓላስ፣ ቦርንመዝ ከብራይተን፣ ኤቨርተንቨርተን ከብሬንት ፎርድ እንዲሁም ፉልሃም ከወልቨርሃምተን ጋር ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ ይጫወታሉ፡፡

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን የደረጃ ሰንጠረዥ ሊቨርፑል በ28 ነጥብ ሲመራ ማንቼስተር ሲቲ በአምስት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ23 ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል።

Exit mobile version