የሀገር ውስጥ ዜና

ወደ አውሮፓና አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል የተሰጠ ውክልና የለም – የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

By amele Demisew

November 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ዘርፍ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል ውክልና አለመስጠቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለሥራ ዜጎችን እንልካለን በማለት የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

ካናዳን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ለሥራ ዜጎችን እንልካለን፤ ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ፍቃድ አግኝተናል በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሕገ-ወጥ ማስታወቂያዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት እየዳረጉ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

መሰል የማጭበርበር ተግባር እየፈፀሙ የሚገኙ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

ዜጎች በስምሪቱ ተጠቃሚ ለመሆን ሕጋዊ አማራጮችን ብቻ በመጠቀም ከአላስፈላጊ ወጪ፣ እንግልት እና ከሌሎች አስከፊ አደጋዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል።

ዜጎች የሁለትዮሽ ስምምነት በተፈረመባቸው መዳረሻ ሀገራት የሥራ ዕድል ለማግኘት lmis.gov.et ማስፈንጠሪያን ተጠቅመው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ላይ በመመዝገብ ደህንነቱ የተረጋገጠ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።