የሀገር ውስጥ ዜና

ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የማዕድን ማውጣት ሥርዓት መዘርጋት ይገባል -ፕሬዚዳንት ታዬ

By amele Demisew

November 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የማዕድን ማውጣት ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ የ2017 ማይንቴክስ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖን በሚሊኒየም አዳራሽ መርቀው ከፍተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷መንግስት የማዕድን ዘርፉን ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት የተሰጠው የማዕድን ዘርፉ መሆኑንና ዘርፉ የተሻለ ውጤት እየተገኘበት እንደሆነም አመላክተዋል።

በዘርፉ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ማዕድን ከማውጣት ባለፈ የእውቀት ሽግግር ማድረግ የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በዓለም ተወዳዳሪነትን ከፍ የሚያደርግና የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚደግፍ መሆኑን እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

ኤክስፖው በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በማሳተፍ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን÷ ዛሬን ጨምሮ ለ4 ቀናት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።

በኤክስፖው በማዕድንና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በታሪኩ ለገሰ