የሀገር ውስጥ ዜና

ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት መልከ ብዙ ስኬቶች ዕውን ያደረገ ፓርቲ ነው – አቶ አደም ፋራህ

By amele Demisew

November 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መልከ ብዙ ስኬቶችን ዕውን ማድረግ የቻለ ፓርቲ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።

በሀሳብ ልዕልና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የተመሰረተ ፓርቲ መሆኑንም ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በፌዴራል ተቋማት ደረጃ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ነው።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፥ ብልጽግና በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ፓርቲ ነው።

ፓርቲው ኢ-ፍትሃዊነት፣ አግላይነት፣ የነጠላ ትርክት የበላይነትና ሌሎች ችግሮችን በሀሳብ ልዕልና ለመፍታት በፅኑ መሰረት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልፀዋል።

ያልተገራ ስሜትና ፅንፈኝነት የሚገራው፣ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው፣ የህዝብ ኑሮ የሚሻሻለው፣ ብሔራዊ ጥቅም የሚከበረው፣ የጥራትና የኢ-ፍትሀዊነት ችግሮች የሚቀረፉት፣ ማህበራዊ ፍትህ የሚነግሰው በሀሳብ ልዕልና ብቻ እንደሆነም ገልፀዋል።

ፓርቲው ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በመቅረፍ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ህልም ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መዳረሻችን ሁለንተናዊ ብልፅግና፣ አንድነት፣ ሕብረ-ብሔራዊነትና አካታችነት ነው ያሉት አቶ አደም ፥ ሁሉም ሰው በደስታና በክብር የሚኖርበት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ መስኮች በሁሉም ለሁሉም በሆነ አግባብ ስኬትን ለማረጋገጥ እየተጋን ነው ብለዋል።

በጋራ ከሰራን ሀገራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻልም የፓርቲው የአምስት ዓመታት ጉዞ በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።

በበሳልና ብቁ መሪ፣ በቁርጠኛ አመራርና አባላት እንዲሁም በህዝብ ድጋፍ ታጅቦ በፈተናዎች ሳይዛነፍ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት መቻሉ፣ የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ መጀመሩ፣ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝም እየተገነባ መሆኑ፣ ምርታማነትን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ዕውን ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ከስኬቶቹ መካከል በዋቢነት ገልፀዋል።

በኢኮኖሚ መስኮች በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደር ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲሁም በማህበራዊ መስኮች የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የተከናወኑ የማህበራዊ አገልግሎት ተግባራትን ጠቅሰዋል።

በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ረገድም በዓለም መድረክ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው ፥ ወዳጅ ሀገራት ማብዛትና የብሪክስ አባልነትን ለአብነት አንስተዋል።

በአጠቃላይ ብልፅግና በተመሰረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መልከ ብዙ ስኬቶች ያስመዘገበ ፓርቲ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ስኬቶችን ለማስቀጠልና ሀገራዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ረጅም ጊዜ የሚፈልግና ውስብስብ ቢሆንም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሀሳብ ልዕልና እየተመራ ዜጎች በክብር የሚኖሩባት ሀገር ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር ህልሙን ዕውን እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ህዝቡ እያሳየ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡