Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት መልከ ብዙ ስኬቶችን ዕውን ያደረገ ፓርቲ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መልከ ብዙ ስኬቶችን ዕውን ማድረግ የቻለ ፓርቲ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንትና በም/ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ነው።

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ÷ብልጽግና በሃሳብ ልዕልና የሚያምን፤ ኢ-ፍትሃዊነት፣ አግላይነት፣ የነጠላ ትርክት የበላይነትና ሌሎች ችግሮችን በሃሳብ ልዕልና ለመፍታት በፅኑ መሰረት ላይ የተመሰረተ ፓርቲ መሆኑን ገልፀዋል።

ያልተገራ ስሜትና ፅንፈኝነት የሚገራው፤ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው፣ የህዝብ ኑሮ የሚሻሻለው፣ ብሔራዊ ጥቅም የሚከበረው፣ የጥራትና የኢፍትሀዊነት ችግሮች የሚቀረፉት፣ ማህበራዊ ፍትህ የሚነግሰው በሃሳብ ልዕልና ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ፓርቲው ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በመቅረፍ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሕልም ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

“መዳረሻችን ሁለንተናዊ ብልፅግና፤ አንድነት፣ ሕብረ ብሔራዊነትና አካታችንተ ነው” ያሉት አቶ አደም÷ ሁሉም ሰው በደስታና በክብር የሚኖርበት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ መስኮች በሁሉም ለሁሉም በሆነ አግባብ ስኬት ለማረጋገጥ እየተጋን ነው ብለዋል።

በጋራ ከሰራን ሀገራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻልም የፓርቲው የአምስት ዓመታት ጉዞ በተግባር ማሳየቱን ነው ያስረዱት፡፡

በበሳልና ብቁ መሪ፣ በቁርጠኛ አመራርና አባላት እንዲሁም በህዝብ ድጋፍ ታጅቦ በፈተናዎች ሳይዛነፍ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

የፖሊቲካ ምህዳር ማስፋት መቻሉ፣ የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ መጀመሩ፣ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝም እየተገነባ መሆኑ፣ ምርታማነትን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳራነትን ዕውን ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ከስኬቶቹ መካከል በዋቢነት ገልፀዋል።

በኢኮኖሚ መስኮች በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደል ልማት የተመዘጉ ስኬቶች እንዲሁም በማህበራዊ መስኮች የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የተከናወኑ የማህበራዊ አገልግሎት ተግባራትን ጠቅሰዋል።

በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ረገድም በዓለም መድረክ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው÷ ወዳጅ ሀገራት ማብዛትና የብሪክስ አባልነትን ለአብነት አንስተዋል።

በአጠቃላይ ብልፅግና በተመሰረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መልከ ብዙ ስኬቶች ያስመዘገበ ፓርቲ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም ስኬቶችን ለማስቀጠልና ሀገራዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.