Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ትሠራለች – ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የፖለቲካ እና ፀጥታ ኮሚቴ ሊቀመንበር አምባሳደር ደልፊን ፕሮንክ የተመራ የአምባሳደሮች ልዑካን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት የረዥም ጊዜ ጠንካራ ስትራቴጂክ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ሕብረቱ በኢኮኖሚ መስክ ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በሀገራዊ ምክክር፣ በሽግግር ፍትሕ እና የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ሒደት ዙሪያ ለኮሚቴው ገለጻ ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያውያን ላይ የጣለውን የቪዛ ገደብ ለማንሳት የተግባር እንቅስቃሴ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር በቀጣናው ሽብርተኞችን በመዋጋት እና በፍልሰት ዙሪያ ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

የአውሮፓ ሕብረት የፖለቲካ እና ፀጥታ ኮሚቴ ሊቀመንበር እና የሕብረቱ የውጭ ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር አምባሳደር ደልፊን ፕሮንክ በበኩላቸው፤ ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ የደህንነት ችግር የአውሮፓ ችግር ነው ያሉት አምባሳደሯ፤ ህብረቱ በቀጣናው እና በአሕጉሩ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

Exit mobile version