Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ተፈናቃይ ነን በማለት በሀሰተኛ ሰነድ ቤትና ድጎማ በመውሰድና በማስወሰድ ወንጀል የተከሰሱ ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ተፈናቃይ ነን በማለት የመኖሪያ ቤትና ድጎማ በመውሰድና በማስወሰድ በመንግስት ላይ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 20 ግለሰቦች የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው።

በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠባቸው ብርሃኑ ግርማ፣ ደረጄ ጌታቸው፣ ዱቦክ ፉፋ፣ ሙሳ አብዲን ጨምሮ 20 ተከሳሾች ናቸው።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 696 (ሐ) ስር የተመለከተውን እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር 4፣ አንቀጽ 23 (2.3) እና አንቀጽ 32 (3.2) ላይ የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህም በአንደኛ ክስ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ከሶማሌ ክልል በግጭት ምክንያት ከኦሮሚያ አዋሳኝ የተፈናቀሉ 1 ሺህ 854 ዜጎች የተፈናቃይ ኮሚቴ ሆነው ሲሰሩ ከአደጋ ስጋት መከላከል ኮሚሽን በተጻፈ የእርዳታና ድጎማ ደብዳቤ መነሻ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በወቅቱ በኮዬ ፌጬ አካባቢ ለተፈናቃዮች ቤት እንዲሰራ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ለተፈናቃዮች የድጋፍና ድጎማ ስራ ሲጀምር በጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም ተፈናቃይ ያልሆኑ ግለሰቦች በሀሰተኛ ጊዜያዊ መታወቂያና ሰነድ እንዲካተቱ አድርገዋል በሚል ተጠቅሷል።

በተለይም ተፈናቃዮችን የመደጎምና የመኖሪያ ቤት የመስጠት ሂደት ውስጥ ተከሳሾች ተፈናቃይ ነን በማለት የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማቅረብ በማጭበርበር በእርዳታ ድጎማው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉም በክሱ ዝርዝር ላይ ተመላክቷል።

በሌላኛው ክስ ደግሞ በተለያየ ጊዜ ሀሰተኛ የተፈናቃይ መታወቂያዎችን እና ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ካምፓስ የተሰጡ የሚመስሉ ሀሰተኛ ሰነዶችን በተለያዩ ስም ዝርዝሮች በማቅረብ ተሳትፎ ያላቸው ተከሳሾች መኖራቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር ተፈናቃይ ሳይሆኑ ተፈናቃይ እንደሆኑ የሚገልጹ ቅጾችን በመሙላት እና በማስሞላት ጭምር ባደረጉት ተሳትፎ በኮዬ ፌጬ አካባቢ እያንዳንዳቸው 705 ሺህ 225 ብር ከ04 ሳንቲም የሚገመት መኖሪያ ቤት በመውሰድ እንዲሁም 19 ሺህ 600 ብር ድጎማ በተለያዩ ጊዜ በመቀበል በተፈጸመ የማጭበርበር የሙስና ወንጀል ድርጊት በመንግስት ላይ 8 ሚሊዮን 697 ሺህ 876 ብር ከ08 ሳንቲም ጉዳት አድርሰዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን ሚና ጠቅሶ ክስ መስርቶባቸው ነበር።

ክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸው በኋላ ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ 14 የሰው ምስክሮችንና ለወንጀሉ መፈፀም ያስረዳሉ ያላቸውን አባሪ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ ተከሳሾች በቀረቡባቸው የክስ ድንጋጌዎች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ የሁለተኛ ክስ ጭብጥ ከአንደኛ ክስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ጠቅሶ ሁለተኛ ክስ ከአንደኛው ክስ ጋር እንዲጠቃለል አድርጓል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ መርምሮና ከዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ጋር አመዛዝኖ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል አለመቻላቸውን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ በይደር ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version