Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአቶ አባተ አበበ ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸም የተከሰሰው ተስፋዬ ሆርዶፋ በሁለት ክሶች እንዲከላከል ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የግድያና የከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በአቶ አባተ አበበ ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸም የተከሰሰው ተስፋዬ ሆርዶፋ በሁለት ክሶች እንዲከላከል ብይን ሰጠ።

የፍትህ ሚኒስቴር የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ ከባድ ግድያ ወንጀል ማለትም የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና የጦር መሳሪያ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ሁለት ክሶችን መስርቶበት ነበር።

በዚህም ተከሳሹ ተስፋዬ ሆርዶፋ ከአዲስ አበባ ከተማ እና ከገላን ከተማ ፍቃድ ካወጣባቸው አጠቃላይ ሁለት ሽጉጥ ውጪ ፍቃድ ያልወጣበትን ሌላ ህገወጥ ሽጉጥ በተሽከርካሪው ውስጥ ደብቆ በመያዝ በታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ኤድናሞል ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ላይ አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በ3 ጥይት በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረግ ህገወጥ ሽጉጡን ይዞ አምልጦ እንደነበር እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቅሶ ዝርዝር ክስ ቀርቦበታል።

ዐቃቤ ሕግ በክሱ የሰው ምስክር ዝርዝርና የተለያዩ ገላጭና አስረጂ የፎረንሲክ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሸ ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰውና ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለፈሙን ገልጾ የዕምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮችን አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን መርምሮ በክሱ ላይ የተገለጸው ወንጀል መፈጸሙን በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ መረጋገጡን ጠቅሶ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ ተከሳሹ በቀረበበት በሁለቱም ድንጋጌዎች ስር እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃ ካለው ለመጠባበቅ ለታህሳስ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version