የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያና ቻይና መካከል በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

By ዮሐንስ ደርበው

November 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና ቻይና መካከል በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት መፈረሙን የሥራ ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል አስታወቁ፡፡

ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ጥምረት ለጋራ እድገት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የገለጹት ሚኒስትሯ÷ ከቻይና መንግሥት ጋር የመግባቢያ ስምምነቱ የተፈረመው ከዓለም የቴክኒክና ሙያ ልማት ጉባዔ ጎን ለጎን ነው ብለዋል፡፡

የሁለትዮሽ ስምምነቱ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ትብብር በመፍጠር ዜጎችን በማብቃት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር፣ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማትን የማሳደግ ዓላማ እንዳለውም አብራርተዋል፡፡

ከቻይና ትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ይህ ስምምነት የቤልት ኤንድ ሮድ አካልና የቻይና አፍሪካን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡