Fana: At a Speed of Life!

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ስራ ለማስገባት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክን ሥራ ለማስጀመር የኢንተርኔት ኔትወርክን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፊልሞን ተረፈ አስታወቁ።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ ከኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ሪጅን ጋር በመነጋገር የኢንተርኔት መሥመር ዝርጋታ ሥራውን የማጠናቀቅ ተግባር ተከናውኗል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የፓርኩን የኤሌክትሪክና የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር ለመፍታት ያልተቆጠበ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በፓርኩ ውስጥ የውሃ አቅርቦት እንዲሟላ ኮርፖሬሽኑ 60 ሚሊየን ብር ለመቐለ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ክፍያ በመፈፀም የኮንትራት ውል የሚፈፀምበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በኤሌትሪክ ሃይል በኩልም ከዚህ ቀደም ወደ ፓርኩ ተዘርግቶ የነበረው መስመር ከፍተኛ የሀይል መቆራረጥ ይታይበት እንደነበር አስታውሰው፤ ችግሩን ለመፍታት በቂ ሃይል ለማግኘት ኮርፖሬሽኑ 34 ሚሊየን ብር ለመቐለ የኤሌትሪክ ሃይል አገልግሎት ክፍያ መፈጸሙን አመልክተዋል።

በመቐለ ሰብስቴሽን የተፈጠረውን ችግር ለማቃለልም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም አቶ ፊልሞን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.