የሀገር ውስጥ ዜና

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች የቀረጥ ጉዳይ!

By ዮሐንስ ደርበው

November 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖች 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ይከፈልባቸው የነበረው 5 በመቶ እንዲሆን መደረጉን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የታክስ ፖሊሲ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙላይ ወልዱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እያበረታታች ነው፡፡

በተለይም መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ የሚገጣጥሙ አካላትን እያበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለአብነትም ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ተበታትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሀገር ውስጥ አምራቾች የሚገጣጠሙት ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ለእነዚህ የሀገር ውስጥ አምራቾች ከለላ በመስጠት ዘርፉን ማበረታታት ወይም ከውጭ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የሚገቡትን በሀገር ውስጥ በሚገጣጠሙት ለመተካት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመሆኑም በውጭ ሀገር ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች አምሥት በመቶ ታክስ እንዲከፍሉ ተወስኖ ወደ ሥራ መገባቱንም አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አንጻር ለኤሌክትሪክ መኪኖች የሚያገለግሉ ቻርጀሮች እና ተያያዥ ጉዳዮች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው