Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ስማርት ከተሞች ኢንቨስትመንት ፎረም ሽልማት ተበረከተለት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ስማርት ከተሞች ኢንቨስትመንት ፎረም ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

ሽልማቱ በኮሪደር ልማት ከተማይቱን ለነዋሪዎቿ እና ለእንግዶቿ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ በአጭር ጊዜ የተገኘውን አመርቂና ውጤታማ ተግባር መሰረት በማድረግ እና በአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ እየተተገበረ ያለውን ተምሳሌታዊ ተግባር በማስመልከት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም “ሰው ተኮር ስማርት ከተሞች ለትውልድ ግንባታ” በሚል ሃሳብ በከተማይቱ ተግባራዊ በመደረጉ እና ዘመናዊና ምቹ ከተማን ለመፍጠር የእግረኛ እና የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች መንገዶች ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባታቸውን መሰረት በማድረግ መሆኑም በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን በማዘመንና ስማርት በማድረግ ውብ፣ ፅዱና ለኑሮ ምቹ ብሎም የአፍሪካዊያን ኩራትና የዓለም የዲፕሎማቲክና የኮንፍረንስ እንዲሁም የቱሪዝም ማዕከልነቷን ይበልጥ ለማጉላት በኮሪደር ልማት በተሰራው አኩሪ ስራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤን በመወከል ኬንያ ናይሮቢ ሽልማቱን የተቀበሉት አቶ መኮንን ያኢ ተናግረዋል፡፡

ሽልማቱ ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ በመሆኑ ሽልማቱን ላዘጋጁ አካላት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ህዝብ ስም ምስጋና ማቅረባቸውንም የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡

Exit mobile version