Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

“ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024” ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየም ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) “ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ሁዋንጃን የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተከፈተ።

የአረንጓዴ ትራንስፖርት ግንባታን ለማበረታታት እና የዘርፉ ተዋንያንን ለማነቃቃት ያለመውን ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከፍተውታል፡፡

በሲምፖዚየሙ የተለያዩ አስመጭዎች፣ ገጣጣሚዎች እንዲሁም በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሠረተ ልማት አምራቾች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ታዳሽ ሀይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በማስፋት እና በፖሊሲም ጭምር በማስደገፍ ለአረንጓዴ ትራንስፖርት ስኬታማነት እየሰራች ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ሰዓት የአረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ለዚህም የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ውጤታማ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በ10 ዓመቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፖሊሲ ላይ ለታዳሽ የትራንስፖርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሲምፖዚየሙ ጎን ለጎን የተለያዩ ሀገራት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉባቸው የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል።

ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየሙ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አማካኝነት መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

በሳሙኤል ወርቃየሁ እና ሰለሞን ይታየው

Exit mobile version