አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ሱቅ የተቃጠለባቸው ነጋዴዎችን በጊዜያዊነት መልሶ ለማቋቋም የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
የአሥተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ድጋፉን ሲያስረክቡ ባደረጉት ንግግር÷ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መልሶ እስኪገነባ ሱቅ ለተቃጠለባቸው ነጋዴዎች የመስሪያ ቦታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ከተደረገው የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ በተጨማሪ የአይነት እና የቴክኒክ ድጋፎችን እናደርጋለን ብለዋል::
በአካባቢው ያለውን ጥግግትና መጨናነቅ በዘላቂነት በመቅረፍ፣ የተሽከርካሪ መንገድን በማካተት እንዲሁም ለአደጋ ተጋላጭ በማያደርጋቸው መልኩ በዘላቂነት በአክሲዮን ተደራጅተው ደረጃውን የጠበቀ የገበያ ማዕከል መገንባት እንዲችሉ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ድጋፉን የተቀበሉት የአካባቢው ነጋዴ ተወካዮች በበኩላቸው አስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ እና ክትትል አመስግነው ድጋፉ በፍጥነት ወደ ስራ እንድንገባ ያስችለናል ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡