አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ሰላሌ-ደራ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ለማድረግ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ሃሳብ እንዳሉት ፥ ራሱን “ፋኖ” ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድንና ሸኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡
ሁለቱም የራሴ የሚሉትንም የጠላቴ የሚሉትን በአምላክ አምሳያ የተፈጠረውን ክቡር የሰው ልጅ ህይወትን አውሬ እንኳን በማይፈጽመው መልኩ በአስከፊ ሁኔታ በሁሉም አማራጮች ይገድላሉ ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ -ደራ አካባቢ ጽንፈኛው ቡድን የፈፀመው የአረመኔነት ተግበር ይህንኑ የሚያመለክት ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
ይህ ፈጽሞ ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አፀያፊ ድርጊት መወገዝ አለበትም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ዓላማቸው ሁለት ነው፤ አንዱ ዓላማ በዚህ አሰቃቂ ድርጊት አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፤ በዚህም እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳካት ነው ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
ሌላኛው ዓላማቸው በዚህ ኢ-ሞራላዊ ድርጊታቸው በህዝብ ዘንድ ፍርሃት በማንገስ ያሻቸውን ማድረግ ነው ፤ ይህ ደግሞ ሞታቸውን ያፋጥነዋል እንጂ የሚሳካ አይደለም ብለዋል፡፡
ቅዥትና እኔ ብቻ የሚል ጫፍ የረገጠ ጽንፈኝነት የሚወልደው በመሆኑ እንዲህ አይነት እኩይ ፍላጎት መቼም ቢሆን ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን አይሳካም ነው ያሉት።
የአንድን ማህበረሰብ ልብ መግዛት የሚቻለው ምክንያታዊ በመሆንና የማህበረሰቡን ህግጋትና ሞራላዊ እሴቶች በመጠበቅ ነው፤ ለማመን የሚከብደን ኢ-ሞራላዊ ድርጊት በመፈፀም በዓለማችን የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የቆመለትን ግብ ያሳካ የለም ሲሉም ገልጸዋል።
ለጊዜው አንዳንዶቹ ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች አንድን ውጥን ያሳኩ ይመስሉ ይሆናል ፤ ይህ እንዳልሆነ የፋሽስቶች ታሪክ ምስክር ነው ሲሉም አስታውሰዋል።
በሁለቱም አቅጣጫ ሰሞኑን በሰላሌ-ደራ ላይ የተፈፀመው እጅግ ሊወገዝ የሚገባው ዓይነት ሰውኛ ያልሆኑ ድርጊቶች በመፈጸም አማራና ኦሮሞን ለመጨረስ ያልተሞከረበት ጊዜ የለም ነው ያሉት።
ግን ሁሉም አልተሳኩም ብቻ ሳይሆን በዚህ ዓይነት ኢ-ሞራላዊ ሁኔታ መቼም ቢሆን አይሳካም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ምክንያቱም የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሚዛናዊ፣ ትርፍና ኪሳራን ለይቶ በምክንያታዊነት አቋም የሚወስድና ወደ ድርጊት የሚገባ ነውና ሲሉም ነው የገለጹት።
ሸኔና ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ በሚፈጽሙት አሠቃቂ ድርጊቶች ሁለቱን የተወለዱ፣ የተገመዱ፣ ከሌሎች ወንድም እህቶቻቸው ጋር በመሆን በከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ያፀኑትን ህዝቦች በማጋጨት የትኛውንም ዓይነት እኩይ ፍላጎት ማሳካት አይቻልም ሲሉም ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ድርጊቱን አውግዘዋል።
የጽንፈኞች ፍላጎት ከማፍረስና ብጥብጥ ከመፍጠር የተሻገረ አይደለም ፤ ፍላጎታቸው የህዝብ ጥቅምና መብት ማስከበር ቢሆን ለምን ንጹሃንን ፣ ምስኪን ራሳቸውን መካለከል የማይችሉ ሰዎችን ይገድላሉ ፣ ያርዳሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ሴቶች ይደፍራሉ፣ የህዝብና ግለሰቦች ሃብትና ንብረት ያወድማሉ? ዓላማቸው የራሳቸውን እና የሌሎች ሃይሎችን ፍላጎትና ጥቅም ማገልገል ነው ሲሉም ይጠይቃሉ።
በእንዲህ አይነት እኩይ ድርጊት የተሰማሩትን አረመኔዎች መላው ህዝብና መንግስት በተባበረ ክንድ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ስርዓት እንዲይዙ ያደርጋሉም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም ይስተካከላል፤ እየነፈሰ ያለው ሰላምም ይፀናል ብለዋል፡፡