የሀገር ውስጥ ዜና

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ግምገማ እየተካሄደ ነው

By yeshambel Mihert

November 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በአርባምንጭ ከተማ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየገመገሙ ነው፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ አገኘሁ ተሻገር÷ በአርባምንጭ ከተማ በዓሉ እንዲከበር ሲወሰን መሰረታዊ መነሻዎች ነበሩት ብለዋል፡፡

ራስን በራስ ለማስተዳደር የተጠየቀው ጥያቄ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተመለሰበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ከ76 ብሔር ብሔረሰቦች 32ቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መገኘታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አርባምንጭ በየጊዜው እያደገ የሚገኝ ከተማ መሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰት ያለበት መሆኑ ተመራጭ እንዳደረገው ገልፀዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዓል በመሆኑ በድምቀት ለማክበር ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ ጠቅሰው÷ በዓሉ መከበሩ የክልሉን አቅም እና ፀጋ ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው÷ በዓሉን በተሻለ እና ለሀገር ትምህርት በሚሆን መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ውይይቱም የተሰሩ ስራዎችን ለመገምገምና በቀሪ ስራዎች ዙሪያ ለመነጋገር እና የመስክ ጉብኝት ለማድረግ ያለመ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡