የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በዓለም የሙያና ቴክኒክ ትምህርት ልማት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው

By Melaku Gedif

November 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በቻይና ቲያንጂን እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም የሙያና ቴክኒክ ትምህርት ልማት ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው።

ወ/ሮ ሙፈሪሃት በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ የበርካታ ወጣቶች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማትን ዋና ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሁለንተናዊ ዘላቂ ልማትን ለማምጣትና የሰው ሃብት ልማት መር ኢኮኖሚ ለመዘርጋት እየሰራች መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር አያይዞ በመሰራቱ ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሀገራት በጋራ እየተፈተኑበት የሚገኘውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት የጋራ ሥራ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆኗን ገልጸው÷ ለዚህም በቅርቡ ያዘጋጀቻቸውን ዓለም አቀፍ መድረኮች በማሳያነት አንስተዋል።

ከቻይና መንግስትና ከተለያዩ ባለድርሻዎች በተሰሩ የትብብር ሥራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ