የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና – የሰርክ ትጋት… የ30 አመታት ጉዞ

By Melaku Gedif

November 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብዙሃን ሀሳብ ማዕከል፣ ትናንትን አስታዋሽ፣ ዛሬን ተግቶ ነገን አላሚ፣ ለወቅታዊ እና አዳዲስ መረጃዎች ቀዳሚ ተመራጭ ሚዲያ ነው ፋና።

የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አጀንዳዎች ማብለያ፦ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠሪያ መስፈንጠሪያም ሆኖ እያገለገለ ነው።

ማዳመጥ፣ መደመጥ፣ ጉዳይ ከባለ ጉዳይ፣ ለባለ ጉዳይ፣ ሁሌም በለውጥ እና በትጋት ውስጥ፣ በየእለቱ በማሻሻያ ሂደት ለሶስት አስርት አመታት በከፍታ የዘለቀ ሚዲያ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ።

ሕዳር 12 ቀን 1987 ዓ.ም ልክ በዛሬው እለት ከ30 አመታት በፊት በድምጽ ወደ አድማጮቹ የደረሰው ፋና ዛሬ የምስረታ ልደቱ ነው።

እንኳን አደረሰን፣ አደረሳቸሁ።

ከሬዲዮ ፋና እስከ ፋና ቴሌቭዥን፣ ከዲጂታል ሚዲያው እድገት እኩል ተምዘግዝጎ ለፋና ፖድካስት ስርጭት የደረሰ ተቋም ሆኗል።

30 አመታት በትውልድ ቅብብል – በይዘት እና ቅርጽ ማሻሻያ በኢትዮጵያ ሚዲያ ውስጥ የራሱን ደማቅ አሻራ አሳርፏል፣ እያሳረፈም ይገኛል።

ህብረ – ብሔራዊት በሆነች ኢትዮጵያ ደግሞ ብዙሃን ሀሳብ ማስተናገጃ፣ የሁሉም ድምፅ ባለቤት፣ የህዝብ ሚዲያ አስፈላጊነቱ የግድ ይሆናል።

ኢትዮጵያዊ እሴትን በመገንባት፣ አቀራራቢ ትርክቶችን የማፅናት ግዙፍ ሃላፊነት ከሚዲያዎች ይጠበቃል፤ ፋና ይህንን ኃላፊነት በትጋት እየተወጣ ነው።

ፋና ሀገራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ እና ከባቢያዊ አጀንዳዎችን በሚዛናዊነት በማስተናገድ የመረጃም የመዝናኛም ማእከል ነው።

በሁሉም የመረጃ ማጋሪያ አማራጮች ከሚዲያ ተቀያያሪነት (ዳይናሚክስ) ጋር እራሱን እያዘመነ እና እያስማማ ከአንጋፋ የሬዲዮ ስርጭቱ እስከ ተወዳጅ እስከሆነበት የቴሌቪዥን አማራጭ እንዲሁም በዲጂታል ምርጫቹሁ ድረስ በትጋት መስራቱን ቀጥሏል።

ከሀገራዊ የልማት ስኬቶች ጀርባ፣ ከፈተናዎች መሻገሪያ ጥበብ ማሳያ ሆኖ የሚጠበቅበትን የሀገር ካስማ ይፀና ዘንድ፤ ለሀገር ይበጃል ባላቸው ጉዳዮች ሀላፊነቱን እየተወጣም ነው።

በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ሚና በመወጣት የበለፀገች ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት፤ ዜጎቿ በሀገራዊ የአንድነት ትርክት የተግባቡ፤ ምጣኔ ሀብቷ ድህነትን አሽቀንጥሮ የጣለ ለቀጣናው የምትተርፍ የምትደመጥና የምትፈለግ ኢትዮጵያ እንድትሆን ስራ ላይ ይገኛል።

ፋና ለአካባቢያዊ ስርጭት ለህብራዊነታችን ትኩረት መስጠቱ የክልል ኤፍ ኤሞቻችን የከባቢያዊ የህብረተሰቡ ጥያቄ በራሱ አንደበት ተናግሮ በራሱ ቋንቋ መፍትሄ እንዲቀመጥለት መስራቱ የሚጠቀስ ነው።

ይህም የማህበረሰብ ንቃተ ህሊናን በማሳደግ ለሀገራዊ ሁለንተናዊ እመርታ ከገጠር እስከ ከተማ ጡብ እንዲያቀብል ያደርገዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት፣ ለህዝብ ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ የሚመለከታቸው አካላት በቃ መፍትሄ እንዲሰጡ በመሞገት ተጠያቂነትን እስከ ማስፈን የደረሰ ማጋለጥ እና ማሳጣት አከናውኗል።

ትናንት ትንሽ ነዉ ነገችን ግን ብዙ ነዉ እኛ እናንተን እያገለገልን ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ ተደማጭነት፣ መሪነት እና ተደራሽነትን ማረጋገጥ መዳረሻ ህልማችን ነዉ።

ብዙ ነን፣ ብዙም አለን እንደ ሀገር የተቸርነዉን ፀጋ በብዝሃነታችን ለብዙሃን ስኬት እንዲሆን መረጃ እንሰጣለን፣ ለዉጤታማነት እንቀሰቅሳለን፣ ለሀሴትም እናዝናናለን። ቁምነገርም እናስጨብጣለን።

ለጉዞዉ ትናንት አብረን ነበርን እጅግም እናመሰግናለን ለከርሞዉም ደግሞ ያድርሰን ስንል የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት እውን እንዲሆን የሁላችንንም ስክነት፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍና፣ ማካፈል ይፈልጋልና፤ እኛ ያለንን አንሰስትም የእናንተም የተለመደ ሀሳብ ለተሻለ ትጋት ያበረታናል እና አብራችሁን ትዘልቁ ዘንድ ምኞታችን ነዉ።

ለተሻለ ስኬት ትጋት ብርታት ትሰጡን ዘንድም እንጠይቃለን።

እንኳን ለ30ኛ አመት አደረሰን፤ አደረሳችሁ።