ስፓርት

ሊድስ ዩናይትድ ከ16 አመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ተመለሰ

By Tibebu Kebede

July 18, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሊድስ ዩናይትድ ከ16 አመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሱን አረጋግጧል።

የዮርክሻየሩ ክለብ ከረጅም አመታት በኋላ ከሻምፒዮንሺፑ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ዳግም ተመልሷል።

ትናንት ምሽት ተከታዩ ዌስትብሮምዊች አልቢዮን በሃድስፊልድ ታዎን 2 ለ 1 ተሸንፏል።

ይህን ተከትሎም በአርጀንቲናዊው ማርሴሎ ቢዬልሳ የሚመራው ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ዳግም መመለሱ ተረጋግጧል።

ሊድስ ዩናይትድ በ44 ጨዋታዎች 87 ነጥብ የሰበሰበ ሲሆን የሻምፒዮን ሺፑ አሸናፊ ለመሆን ከቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹ አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘት በቂው ይሆናል።

በሚከተሉት የእግር ኳስ ፍልስፍና በርካቶችን መማረክ የቻሉት ቢዬልሳ በዮርክሻየሩ ክለብ ሁለት የውድድር አመታትን አሳልፈው ክለቡን ወደ ትልቁ ሊግ አምጥተውታል፡፡

የቡድናቸውን ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊግ መመለስ በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ የሊድስ ደጋፊዎችም ደስታቸውን አደባባይ ወጥተው ገልጸዋል፡፡

የሊድስ ዩናይትድ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ዳግም መመለስ ከላንክሻየሩ ማንቼስተር ዩናይትድ እና ከመርሲሳይዱ ሊቨርፑል ጋር የሚኖረውን የባላንጣነት ስሜት ተጠባቂ ያደርገዋል፡፡

16 አመታትን ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዶ በሻምፒዮን ሺፑ እንዲሁም በአንድ አጋጣሚ በሊግ 1 ያሳለፈው ሊድስ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመመለስ 15 አሰልጣኞችን ሞክሮ አልተሳካለትም ነበር፡፡

ባለፈው አመት በደርሶ መልስ ጨዋታ ዳግም ለመመለስ ያደረገው ሙከራም ሳይሳካለት መቅረቱ የሚታወስ ነው፡፡

“እብዱ” በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁ ቢዬልሳ ክለቡን ዳግም ወደ ትልቁ ሊግ በመመለስ የደጋፊዎችን የልብ ትርታ መልሰዋል፡፡

ሊድስ ዩናይትድ በፈረንጆቹ 2004 ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱ የሚታወስ ነው፡፡

በሻምፒዮን ሺፑ 45 ጨዋታ የተጫወተው ዌስትብሮም 82 ነጥቦች ሲኖረው ተከታዩ ቤንትፎርድ ደግሞ በ44 ጨዋታዎች 81 ነጥቦችን ሰብስቧል።

ዌስትብሮም ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል ከኪው ፒ አር ጋር በሚያደርገው ቀሪ አንድ ጨዋታ ማሸነፍ እና ሁለት ጨዋታ የሚጫወተው ቤንትፎርድ ነጥብ እንዲጥል መጠበቅ ይኖርበታል።

በአንጻሩ ቤንትፎርድ ከስቶክ ሲቲ እና ባርንስሌይ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ በቀጥታ ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀል ይሆናል።