የሀገር ውስጥ ዜና

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በብቃት ላይ የተመሠረተ አመራር እንዲኖር እየተሰራ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

By Shambel Mihret

November 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በብቃት ላይ የተመሠረተ አመራር እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አስታወቁ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴርና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራሮች ምደባ ብቃትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን እየተሰራ ነው።

የአንድ ሀገር ልማትና ስኬት የሚወሰነው በዋነኛነት በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ላይ በሚያገለግሉ አመራሮች ብቃት እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡

አሁን የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ውጤታማ አመራርን ለማፍራትም ሆነ ሀብትን በውጤታማነትና ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል፡

የአፍሪከ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፥ ጠንካራ አመራር ለመፍጠር ግልጽ የአመራር ልማት ፖሊሲ፣ በስልጠናው የሚለይ የአመራር ልማት ፕሮግራም እንዲሁም ሳይንሳዊ የአመራር ምዘና ስርዓት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሟላ ብቃት ያለውና ቁርጠኛ አመራር በመፍጠር የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች በታሰበው መንገድ ለውጤት እንዲበቁ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

ደረጃውን የጠበቀ ሀገር በቀል ስልጠና መኖሩ ሀገሪቱ የምትፈልገውን አመራር በብዛትና በብቃት ለማፍራት ከማሰቻሉም ባሻገር አመራሮችን በውጭ ሀገር በማሰልጠን የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት እንደሚያግዝም ማብራራታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡