አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአሰሪዎቿ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረትና ገንዘብ የሰረቀችው የቤት ሰራተኛ በቁጥጥር ስር መዋሏን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ስሙ አያት ዞን 1 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን÷ ተጠርጣሪዋ በደላላ አማካኝነት በቤት ሰራተኝነት መቀጠሯ ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዋ ከተቀጠረች በ3ኛው ቀን የግል ተበዳይ ወደ ሥራ በሄዱበት ወቅት አጋጣሚውን በመጠቀም በቤቱ ውስጥ የተቀመጡ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች እንዲሁም የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦችን ሰርቃ መሰወሯን የፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
የግል ተበዳይ ለፖሊስ ያቀረቡትን ማመልከቻ ተክተሎ በተደረገ ክትትል ተጠርጣሪዋ የወንጀል ድርጊቱን ከፈፀመች በኋላ በክፍለ ከተማው ወረዳ 14 አባዶ አካባቢ በአንድ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ ከሰረቀቻቸው ቁሳቁሶች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሏ ተጠቁሟል፡፡
ግለሰቧ በቁጥጥር ስር በዋለችበት ወቅትም የሰረቀቻቸውን የተለያዩ አልባሳት፣ የተለያዩ የሴትና የወንድ ጫማዎች፣ 18 ሺህ የአሜሪካ ዶላርና የሕንድ ሩፒ፣ የተለያዩ የወርቅና ልዩ ልዩ ጌጣጌጦች ይዛ መገኘቷ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በሁለት የተለያዩ ስሞች የነዋሪነት መታወቂያ የተገኘባት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የመሪ ሉቄ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አበበ እንዳሉት÷የግል ተበዳይ ተጠርጣሪዋን ለስራ ሲቀጥሯት ያቀረበችው የተያዥ ፎርም የራሷን ፎቶ በትክክል እንዳይለይ አድርጋ ለጥፋለች፡፡
ሕብረተሰቡ የቤት ሰራተኛ ሲቀጥር በሕጋዊ መንገድ በቂ ተያዥ በማስቀረብ የተያዣቸውን አድራሻና ማንነት በአግባቡ በማጤን መቅጠር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡