አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 13ኛው የአፍሪካ ኢንተርኔት አስተዳደር ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
“ዲጂታል አፍሪካን እውን ለማድረግ ጠንካራ ባለድርሻ አካላትን መገንባት ያስፈልጋል” በሚል መሪ ሐሳብም ዛሬ ከፓርላማ አባላት ጋር ወይይት ተደርጓል።
በዚሁ ወቅትም በአፍሪካ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
በተለይም ደህንነቱ የተጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ በይነ መረብን የሚደግፉ የቁጥጥር እና የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ይገባል ነው የተባለው።
የቁጥጥርና የፖሊሲ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት አንጻር የህዝብ እንደራሴዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ኢንተርኔትን በከተሞች ብቻ ሳይሆን በገጠር ላለው የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባም ተመላክቷል።
አፍሪካ በ2063 ያሰበችበት ለመድረስ በኤ አይ ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች ስለመሆኑም ተገልጿል።
ኮንፈረንሱ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ይካሄዳል።
በታሪኩ ለገሠ