መዋቅራዊ የምጣኔ ኃብት ሽግግርን ለማሳለጥ የልማት አጋሮች ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

By Shambel Mihret

November 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ኃብት ሽግግር ለማሳለጥ የልማት አጋሮች ትብብር ወሳኝ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ተናገሩ።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በተገኙ ውጤቶችና በምጣኔ ኃብታዊ ሽግግር ዙሪያ ከልማት አጋሮች ጋር ምክክር እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ ፓሊሲዎችና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።

አቶ አሕመድ ሺዴ በዚሁ ጊዜ÷ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ኃብት እድገት እውን ለማድረግ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚን ጨምሮ እየተገበረቻቸው ያሉትን የልማት መርሐ ግብሮች አንስተዋል።

ለመዋቅራዊ የምጣኔ ኃብት ሽግግር መሳካት የልማት አጋሮችና ሲቪል ማኅበራት ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

የልማት አጋሮች የምጣኔ ኃብት ሽግግር ግብን ለማሳካት በሚያደርጉት ትብብር አካታችነትን ለማጠናከር እንዲሁም ተጠያቂነትና ግልጸኝነትን ለማስፈን አቅም ይፈጥራል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመድረኩ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሐ ግብርና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም አምባሳደሮች ተገኝተዋል።