አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በመደበኛ ሁኔታ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የበጋው ደረቅ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለሚቀጥሉት 10 ቀናት በሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅ፣ ምሥራቅ፣ መካከለኛው እና የደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚዘወተር ገልጾ፤ አልፎ አልፎ የማስከተል ጥንካሬ እንደሚኖረውም ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡
በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸውም ተነስቷል፡፡
በፀሃይ ሀይል ታግዞ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት በተለይም በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ሰፊ ቦታዎችን የሚያካትት ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል ነው የተባለው፡፡
በሌላ በኩል በመካከለኛው፣ በምስራቅ፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአጠቃላይ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ወላይታ፣ ኮንሶ፣ ጌዴኦ፣ ባስኬቶ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አሌ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ፣ ከፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳዉሮና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ ከሶማሌ ክልል ዳዋ፣ ሊበን፣ አፍዴር፣ ሸበል፣ ኖጎብ፣ ቆራሂ፣ ዶሎ፣ ጃረር እና ኤረር፤ እንዲሁም ሐረሪ ክልል እና ድሬዳዋ አስተዳደር ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ ከክረምት ወቅት ጀምሮ ዝናብ እያገኙ ባሉት አካባቢዎች ማለትም ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ ቄሌም ወለጋ፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ ከጋምቤላ ክልል የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር አኝዋክ እና ማጃንግ ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ከአማራ ክልል በሰሜን፣ ማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር፤ ምስራቅ፤ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም፤ አዊ ዞኖች እና ባህርዳር ዙሪያ፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋህግምራ፤ ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፤ ከትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ፤ የደቡብና የደቡብ ምስራቅና ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ፋንቲ፤ ማሂ፣ ሃሪ፣ ቀልበቲ፣ ሃዉሲ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፤ ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፤ አዲስ አበባ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ ከሶማሌ ክልል የሲቲና እና ፋፋን ዞኖች፤ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለዉ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በዚህም በሚኖሩት ደረቅ ቀናቶች የደረሱ ሰብሎች መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ጠቁሟል፡፡