Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሩሲያ ዩክሬን በአሜሪካ ሚሳኤል ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ ርምጃ እንደምትወስድ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ዩክሬን በአሜሪካ ሰራሽ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል በሞስኮ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት አጸፋዊ ርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች፡፡

ዩክሬን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሰጡት ፍቃድ መሠረት አሜሪካ ሰራሽ ሚሳኤሎችን በትናንትናው ዕለት ወደ ሩሲያ ማስወንጨፏ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ይበልጥ መባባሱ ነው የተነገረው፡፡

በዛሬው ዕለትም ሩሲያ ዩክሬን በአሜሪካ ሰራሽ ሚሳኤል ለፈጸመችው ጥቃት ተመጣጣኝ አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች፡፡

የረጅም ርቀት ሚሳኤል ጥቃቱንም የምዕራባውያን ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ስትል ሩሲያ መወንጀሏን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ድርጊቱ ምዕራባውያን በሞስኮ ላይ የጀመሩት አዲስ የጦርነት ምዕራፍ መሆኑንና ለዚህም በየደረጃው ተመጣጣኝ ርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቃለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምስራቃዊ ዩክሬን እየጨመረ የመጣውን የሩሲያ ወታደሮችን እንቅስቃሴ ለመገደብ የሚያስችል ጸረ-ሰው ፈንጂዎችን ለዩክሬን ለመስጠት መስማማታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ባይደን በዩክሬን ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል ጸረ-ሰው ፈንጅ ለመስጠት ቢስማሙም በዩክሬን በኩል ፈንጂውን የመጠቀም ፍላጎት እንደሌለ ተጠቁሟል።

Exit mobile version