አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል የአከራይና ተከራይ ሕጋዊ ውል ምዝገባ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡
በአዲሱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ 1320/2016 መሰረት የአከራይና ተከራይ ሕጋዊ ውል ምዝገባ ከነገ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
በዚህም በህግ አግባብ የተዘጋጀ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ሰነድ፣ የአከራይና ተከራይ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የመስሪያ ቤት መታወቂያ፣ መንጃ ፍቃድ፣ ፓስፖርት፣ የጥብቅና ፍቃድ፣ የዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ተማሪ የታደሰ መታወቂያ ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶች ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም የመኖርያ ቤት ኪራይ ውሉ የሚመዘገበው በወኪል ከሆነ ሕጋዊ ውክልና የሁለት ምስክሮች የታደሰ መታወቂያ ኦርጅናልና ኮፒ፣ አከራይ የመኖሪያ ቤቱን ለማከራየት የሚያስችል መብት እንዳለው የሚያሳይ ህጋዊ ሰነድ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡
የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ወይም ሰነድ አልባ ይዞታዎች መሆኑን ከሚመለከተው አካል ማስረጃ ወይም በፍርድ አፈጻጸም የተሸጠ ንብረት ሰነድ፣ የተከራየው ቤት በውርስ የተገኘ ሆኖ ስም ዝውውር ካልተፈፀመ የወራሽነት ማረጋገጫ ኦርጂናልና ኮፒ ይዘው በአካል መቅረብ ያለባቸው መሆኑንና ምዝገባው በየወረዳው በሥራ ሰዓት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ምዝገባ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ያላከናወኑ አከራይ እና ተከራዮች በቅጣት ወደ ውል ሥርዓቱ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑንም የሐረሪ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡